ለሕዝቡም ቃሉን ተናግሮ ከፈጸመ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም ገባ። አንድ የመቶ አለቃም ነበረ ፤ አገልጋዩም ታሞ ሊሞት ቀርቦ ነበር። እሱም በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነበር። የጌታችን የኢየሱስን ነገር በሰማ ጊዜ ፥ መጥቶ አገልጋዩን እንዲያድንለት ይማልዱት ዘንድ የአይሁድን ሽማግሌዎችን ወደ እርሱ ላከ። ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስም መጥተው ማለዱት። እንዲህም አሉት “ፈጥነህ ውረድ ፤ ይህን ልታደርግለት ይገባዋል። እርሱ ወገናችንን ይወዳልና ፤ ምኩራባችንንም ሠርቶልናልና።” ጌታችን ኢየሱስም ከእነርሱ ጋራ ሄደ። ወደ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን እንዲህ ብሎ ላከ ፤ “አቤቱ ፣ አትድከም ፤ ከቤቴ ጣሪያ በታች ልትገባ አይገባኝምና። እኔም ወደ አንተ ልመጣ አይገባኝም ፤ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ ፤ ብላቴናዬም ይድናል። የሉቃስ ወንጌል 7 ፥ 1 – 7
እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሽማግሎችን ምልጃ አልናቀም ፤ አልተወምም። የእመቤታችንንም ፤ የቅዱሳንንም ፤ የጻድቃንንም ፤ የቅዱሳን መላእክትንም እንድዚሁ አይንቅም ፤ አይተውምም።
ሰው ክቡር ነበር፡፡ Human was Honor.
“ሰው ግን ክቡር ሲሆን አላወቀም። ልብ እንደሌለው እንደ እንስሳም ሆነ ፤ መሰላቸውም። ሰውስ ንጉሥ ሲሆን አላወቀም። በፈቃዱ ራሱን አዋረደ ፤ ባርያም ሆነ ፤ ጌቶችም ያልሆኑትም ገዙት። ሰውስ ባለጸጋ ሲሆን አላወቀም። ልብ እንደሌለው እንስሳም ሆነ ፤ መሰላቸውም። በፈቃዱ ራሱን ነዳይ አደረገ ፤ ሆዱን አስራበ ፤ ነፍሱንም አስጠማ።” ከቅዳሴ አትናቴዎስ
Human did not know he had honor, and he became like the beasts who have no heart. Human is king, but he do not know it. He debased himself at his own will to become a servant. Those who are not lords ruled over him. Human was rich, but he was unaware of it. He chose to impoverish himself. This pleased him, leaving his stomach hungry and his soul thirsty. From Anaphora of Athanasius
ዝቅ ዝቅ በል
ዝቅ የማለትን ጥቅም ለማወቅ ገበሬን መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። ዘሩን ከዘራ በኋላ ቀና እንዳለ ቢቀር ኖሮ ዘሩ አፍርቶ ምርቱን ማየት አይችልም ነበር። አርሶ አለስልሶ ከዘራ በኋላ ማረም ፣ መኮትኮት ፣ ምርቱ ከደረሰም በኋላ ማጨድ አለበት። እነዚህን ለማድረግ ደግሞ የግድ ዝቅ ፣ ጎንበስ ማለት ያስፈልገዋል። በመጨረሻም ከራሱ ተርፎ ሀገርን የሚመግብ ምርት ያገኛል።


አንተም እንዲሁ በዕውቀት ፤ በሥልጣን ፣ በዝና ወይም በሀብት ከፍ እንዳልክ ከቀረህ ይህ አደጋ ይኖረዋል። ድሮ ተማሪ ፣ ወይም ተራ ሰው ፣ ወይም ደኃ በነበርክበት ወቅት ዝቅ ብለህ ስለነበር ብዙ መልካም ሥራዎችን እየሠራህ እግዚአብሔርን ታስደስተው ነበር። ከዚህ መልካም ሥራህ የተነሣ እግዚአብሔር በበረከቱ ከፍ አድርጎሃል። ነገር ግን ከፍ ከፍ እያልክ ስትሄድ በሰውኛ ወይም በምድራዊ ሒሣብ ሲታይ ብዙ መልካም ነገሮችን የሠራህ ይመስልሃል። እንደ እግዚአብሔር ኃሣብ ከሆነ ግን ብዙም ጠቃሚ ነገሮችን ለራስህ ጭምር ሳትሠራ ከፍ እንዳልክ ታልፋለህ።
ዝቅ ስትል ደግሞ ከፍ ባልክበት ዘመናት ያላየኻቸውን ብዙ ነግሮችን ታያለህ። በተለያዩ ምክንያት መንገድ ላይ የወደቁትን አንተን መሰል ሰዎችን ፤ በተለያዩ ምክንያቶች አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናትን ፣ ተስፋቸው እግዚአብሔርን ያደረጉና የሰው እጅን የሚጠባብቁ ጧሪ የሌላቸው አዛውንቶችን ፣ ሌላው ቀርቶ በምቾት ያሳደግህ መስሎህ በሞግዚትና በጠባቂ የምታሳድጋቸው ፤ አንተ ሳትረዳቸው ቀርተህ በአጉል ወጥመድ ሊገቡብህ የሚችሉትን የገዛ ልጆችህን ፣ የሁሉም መሠረት ገጠር እንደመሆኑ ገጠር ያሉ ደኃ ዘመዶችህን ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ እንደድሮውህ ብትከተለው ከፍ ካሉት ተርታ የሚያሰወጣህ መስሎህ የምታፍርበትን እምነትህን ማየት ትችላለህ። ያኔ መልካም ፍሬ አፍርተህ በማጨድ መልካም ምርት ታገኛለህ። አለበለዚያ ወደድክም ጠላህም በመጨረሻህ ቀን ዝቅ ከማለት በከፋ ሁኔታ ወድቀህ መዘርጋትህ አይቀርም። 
ለወዳጄ ለአእምሮ
ይድረስ ለመሰሌ እእምሮ እንድምን አለህ? ልምዳችን ሆኖ ነው “እንደምን አለህ”አልኩህ እንጂ የሰሞኑ ሁኔታችንን እኔም አንተም እናውቀዋለን። ሰሞኑን ኮሮና በሚባለው ቫይረስ ምክንያት ቤት ውስጥ በመቀመጤ ሰፊ ጊዜ ስላገኘሁ ይህችን ሰላምታ ልጽፍልህ ተነሳሳሁ። በዚህ ዓለም ላይ ችግሮች በዙ። አሁን አሁንማ ከእኛ ቁጥጥር በላይ የሆኑ ነገሮች እየተከሰቱ ጉልበታችንንና ኃይላችን በከንቱ እያበላሹብን ነው። እንዳውም አሉ የሚባሉ አእምሮዎች ለዘላለም እያሸለቡም ነው። ስለአንዱ አስበን ሳናበቃ ሌላ ከበድ ያለ ነገር ይከሰታል። ከእኔ የሚወጣው ኃሣብ ፤ እንኳን ሌላውን እኔን ራሴ ከሞት የሚያስጥለኝ ሆኖ አላገኘሁትም። ጊዜያዊ መፍትሄ ባመጣም እንኳን እምብዛም የሚረዳ አልመሰለኝ። አሰብኩ አሰብኩ አሰብኩ ሌላ አእምሮ መፍጠርና መተካት ፤ በሕይወት ያሉትን አእምሮዎች ማዳን ፤ ሞትን ለዘላለም ማስቆም ካልቻልኩ እኔ ማን ነኝ? ኃይሌና ሥልጣኔስ ምን ያህል ነው?
የሚገርመው ነገር ደግሞ በጣም ጥቂት የሆኑት “መጠቁ” የተባሉት ወንድሞቻችን አእሞሮዎች ሌላውን አእምሮ ለመጥቀም ፤ ግኝት ለማድረግ ያለ ዕረፍት ሲያስቡ ብዙዎቹ ደግሞ ብዙ ወንድሞቻቸው አእሞሮዎች የሚጠፉበትን ያለ ዕረፍት ሲያስቡ መኖራቸው ነው። አንድ ሩቅ ካለ ወዳጄ ጋራ ምናብ ደውዬለት ስናወራ “እኩይ አእምሮዎች ለምን ሌሎች አእምሮዎች የሚሰቃዩበትንና ሚሞቱበትን ኃሣብ ያመነጫሉ?” ብዬ ጠየቅኹት። ምን እንዳለኝ ታውቃለህ? “መልሱ ቀላል ነው ብዙዎች ጓደኞቻችን ኃሣብ ለማመንጨት የሚጨነቁት ብዙ ገንዘብ ወይም ልዩ ክብር ለማስገኘት ነው።” ብሎኝ አረፈው። በጣም ሳቅሁበት። “የዚህ አእምሮ አእምሮው ተነክቷል እንዴ?” አልኩኝ።
ገር ግን ጊዜ ወስጄ ስለ ሁሉም ዓየነት አእምሮዎች ማሰብ ጀመርኩ። በሳይንስ ፣ በፖለቲካ ፤ በትምህርት ፤ በሃይማኖት ፣ በጤና ፣ በባህል ምን አለፋህ በሁሉም መስክ የተሰለፉትን። ለካስ ከላይ የጠቀስኩት ክፉኛ ያፌዝኩበት ወዳጄ ትክክል ነበር። ያለ ዕረፍት የምናስበው ለገንዘብና ለልዩ ክብር ኖሯል። በዚህ ምክንያት ስንት አምሮዎች አለቁ ? እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ። እኛ ከየትና ለምንድነው የተፈጠርነው? ከመምጠቃችን የተነሣ ማን ወይም ምን እንደፈጠረን ሳናውቅ ስለ ብዙ ነገር እናውቃለን። እናስባለን። እንመራመራለን። ግማሾቻችን ለምን እንደተፈጠርን ሳናውቅ ፍጡራን ላይ አተኩረን እንፈላሰፋለን። ግን እኮ ምርምራችን እኛን ከሞት በፍጹም ሊያድነን ወይም የሞት መድኃኒት ማግኘት እንኳን አልቻለም። ሰው የተባለውን ተሸካሚያችንን ይዘን እንሞታለን።
አሁን አሁንማ ሳስበው “ፈጠራ” እያልን የምናቀርበው ትክክል እናዳልሆነ ውስጤ እውነቱን እያወቀው ነው። “ፈጠራ” የሚባለው በዓለም ላይ የሌለን ነገር ካለመኖር ወደ መኖርነት ማምጣት ነው። ታድያ እኛ የላቅን አእምሮዎች እስቲ ምንን ነው ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣነው? መድኃኒት? ቴክኖሎጂ? ያማሩ ልብሶች? ዘመናዊ መጓጓዣዎች? ሚዲያዎች? ዘመናዊ መገናኛዎች? ሰማይ ጠቀስና ጠማማ ሕንፃዎች? ብቻ “አዎ!” ብለኸኝ በሳቅ ልቤን እንዳታቆስለው። እንዚህማ ጥንት እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፣ በመሬት ላይና በውስጧ ያሉትን ውኃና የፀሐይን ኃይል በጨመር መልካቸውንና ቅርፃቸውን ቀየር አድርገን አቀናብረን ያቀረብናቸው ናቸው እንጂ እንደ አዲስ ነገር የፈጠርናቸው አይደሉም። መሬትም ፣ ፀሐይም ሆነ ውኃ የእኛ ውጤቶች አይደሉም። ድሮም ነበሩ አሁንም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ።.
ወንድሜ ሆይ፣ ከዚህ በኋላ እኔ በበኩሌ ስለተፈጠሩት እያሰብኩ ጊዜዬን ከማጠፋ በቅድሚያ ስለ እኔ ማንነት ፤ ስለ ፈጠረኝ ፤ ስለተፈጠርኩበት ምክንያት ለማወቅ ወደ ኋላ ተመልሼ ማሰብና ማወቅ ይጠቅመኛል። በእኔ ኃሣብም እንደምትስማማና ከጎኔ እንደምትሰለፍ ተስፋ አደርጋለሁ። ኮሮና እንዳይዝህ ደግሞ ተጠንቀቅ። Cerebellumህን ፣. ሁሉንም lobeዎችህንና Brain stemህን ቶሎ ቶሎ ቢያንስ ለ20 ሰከንዶች በሳሙና ታጠብ። Frontal lobeህን በእጅህ አትንካ። የግል ንጽሕናህንም ጠብቅ። የእኛ የኃሣብ ምጥቀት የማያድነንና መቼም ይሁን መቼ ከተሸካሚያችን (ከሰው) ጋራ መሞታችን የማይቀር መሆኑን ግን ምን ጊዜም አትዘንጋ። እስከዛውም መልካም መልካሙን ኃሣብ እናምንጭ። መልካም ኃሣብ!!!
ከፍልስፍና ጋራ
ወንድምህ የአንተው ቢጤ አእምሮ
ጩኸት
ጩኸት
እውነተኛ ጩኸት፦ ይህ ጩኸት እውነትን ያዘለ። የተበደለ ፍትህን እንዲያግኝ ጫና ለማሳደር የሚጠቅም ፤ የሕዝብን መልካም ኖሮና የሕዝብን ዕድገት ሊያስከትል የሚችል ፤ በበቂ ሁኔታ ምክንያታዊ ሲሆን ነው። ይህ ጩኸት በእውነት ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ መቼም ይሁን መቼ ውጤት ማምጣቱ የማይቀር ነው። እንስሳትም ይጮኻሉ። ስለ እውነት ነው የሚጮኹት። ለምሳሌ ውሻ ወደ ጌታው ቤት ከቤተሰቡ ውጭ ሰው ሲመጣ ጌታው ሰውየውን ፈቅዶ እስከሚያስገባው ድረስ ይጮኻል። ውሻው በሐሰት አልጮኸም ፤ የሱ እውነት እንግዳ ሰው ወደ ቤት መምጣቱ ነው።፡ወፎች በእውነት ላይ ተመርኩዘው ነው የሚጮኹት። የነእነርሱ ጩኸት እውነቱ ንጋት መምጣቱ ነው። ወንድ ዶሮችም ሌሊት ይጮኻሉ። የሚጮኹበት እውነታቸው ሰዓታቸው ነው። ድመትም ሲርባት።
ሁለተኛው ጩኸት እውነትነት የሌለው የሚፈለገው ለማግኘትና ለማሸነፍ የሚደረግ ጩኸት ከሚታሰውው በላይ የከፋ ይሆናል። ሰይጣን የተሰጠው የመላእክትነት ክብር አልበቃው ብሎ የፈጠርኳችሁ እኔ ነኝ በማለት በሐሰት በመላእክቱ ላይ ጮኸ። ተከታይ መላእክትም አገኘ። ውጤቱ ግን እሱና ተከታዮቹ መላእክት ወደ ጥልቁ ለዘላለም መወርወር ነበር።
ምክንያት አያድንም
ማጣትህ አማራጭ የሌለው ከሆነ ለምን እንጂ አትስረቅ። በምንም መልኩ ቢሆን ያልፋህበትን ሃብት ንብረት በመልካም ፈቃዳቸው በስጦታ ሰዋች ካልሰጡህ በስተቀር ወደ ቤትህ ይዘህ አትግባ። ወይም ደግሞ በዕጦትህ ምክንያት አዝነህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ላይ ፊትህ አዙረህ በቀላሉ ሃብታም ሊያረግህ የሚችል አምልኮ ወይም ተግባር ውስጥ አትግባ። ብትበደል ፣ ፍትሕ ቢዛባብህ ፣ እውነትነት ቢኖርህ እንኳ ጠላትህን ለመግደል ፣ ለመጉዳትም ቢሆን አትሞክር። እግዚአብሔር ያያል ከታገሥክ እግዚአብሔር ይፈርድልሃል። ብትችልማ የበደለህን ይቅርታ ብታደርግለት ዋጋ አገኘህበት። ነገር ግን እግዚአብሔር ትቶኛል ብለህ ተስፋ አትቁረጥ። አስታውስ አንተን የፈጠረህ ጠይቀኸው ወይም ለምነኸው አይደለም። እራሱ ፈቅዶ አንተን በኅሊናው አስቦ ነው። እሱ ደግሞ የራሱን ዕቃ የማይረሳ አምላክ ነው። ሁሉን ነገር ለማድረግ ኃይል ባለህ ወራት ግፍ መፈጸምን ፍራ። የሰው ልጅ ችግሩ ግፍ በሌላው ላይ ፣ በራሱም ላይ ቢሆን ሲፈጽም ምንም አይሰማውም። ተፈጽሞ ከአበቃ በኋላ ነው አእምሮው ጥያቄን የሚያነሣው።” ጅብ ካለፈ ውሻ ጮኸ” እንዲሉ። ግፍ ነፍስን የማቆሸሽ ከፍተኛ ደረጃው ነው።
አስተውል አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ አትብሉ ብሎ እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ጥሰው በሉ። አዳም ሲጠየቅ ሔዋን እንዳሳተችው ሔዋንም ስጠየቅ እባብ እንዳሳታት ፤ መለሱ። የሔዋን ምክንያት እባብ ፤ የአዳም ምክንያት ደግሞ ሔዋን ነበሩ። ምክንያታቸው ፈጽሞ ከሞት ሊያድናቸው እንዳልቻለ ተረዳ። ማንም አሳሳተህ ማን ፤ ወይም ክፉ ሥራህን እንድተፈጽም ምንም አዝዞህ ብትፈጽመውም እንኳን የአዘዘህ ሰው ሊያድንህ አይችልም። ክፉና ደጉን የምትለይበት አአምሮን የሚያክል መሣሪያ ሰጥቶሃልና። ማንም ሰው የተባልን ፣ ሃይማኖት ያለውም ሆነ የሌለው ፤ አመንበትም አላመንበትም ማናችንም ከዓለም ፍጻሜ በኋላ በምድር በነበርንበት ወቅት ያደረግነው እያንዳንዱ ተጋባራችን በፊታችን እንደ መጽሐፍ ተዘርግቶ ይፈርድልናል ወይም ይፈርድብናል። ማንም ምንንም ማዳን አይችልም። እናትና አባት ፣ እህትና ወንድም ፣ ልጅ ፣ የሃይማኖት መሪ ፣ ሐብታም ፣ ባለሥልጣን ፣ አክቲቪስት ፣ የፖለቲካ ድርጅት ኃላፊ ። እኔንም ቢሆን ምክንያት አታደርገኝም። እኔም አንተን ምክንያት ላደርግህ አልችልም።
እኔም ራሴ ስንት እኩይ ሥራ ሠርቻለሁ ፤ በድያለሁ። ግን መተንፈስ እስከቻልኩ ድረስ እንደቸርነቱ ይምረኝ ዘንድ ዛሬ አሁን እለምነዋለህ። እንኳን ተጨማሪ ጥፋት ለመሥራት ለመልካም ሥራ እንኳን ጊዜ ሊያጥረን ይገባል።
ትምህርት ለምን?
በመሠረቱ የትምህርት አስፈላጊነት በኅብረተሰብ ውስጥ ለተከሰቱ ወይም ሊከሰቱ ለሚችሉት ችግሮች መፍትሄ ማግኛ መንገድ ለማግኘት ነው። ብዙዎቻችን ግን ትምህርት ቤት ስንሄድ የነበርነው አሁንም ልጆቻችንን ትምህርት ቤት የምንልከው ከምረቃ በኋላ ኅብረተሰባችን በኑሮው ውስጥ የሚያጋጥመውን ችግር ለመቅረፍ ዝግጁ ለመሆን ሳይሆን ” ሥራ ተይዞ” ደሞዝተኛ መሆን እንዲቻል እያሰብን ነው። ለዚህም ነው በአገራችን ውስጥ የአኗኗር ስልት ብዙ ለውጥ የማያመጣው።
ለምሳሌ በአገራችን ስንት ሰው በኤሌትሪክ ፤ በእርሻ ፤ በውሃ ሃብት ፤ በማዕድን ጥናትና ምርምር ፤ በጤና ፤ በመንገድ ሥራ ፤ በመሃንዲስነት ፤ በዳኝነት ፤ በፖለቲካ ሳይንስ ወዘተ የተመረቀውና “ሥራ” የያዘው? የኅብረተሰቡ ችግር ግን እየ ባሰ እንጂ ሊቀንስ አልቻለም። የመብራት ፣ የእርሻ ፣ የመጠጥ ውኃ ፣ ሕክምና ፣ የፍትሕ መዛባት፤ ትራንስፖርት …….. እስቲ ፍረዱኝ የእርሻ ሚኒስቴር ሰራተኞች በአዲስ አበባ የግብርና ሚኒስቴር
ሕንፃ ከዓመት እስከዓመት ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለው እንዲት ነው የገበሬውን ችግር የሚቀርፉት? አስቡት እስቲ ሁለት በሬዎች በቀንበር ተጠምደው ከሚክሲኮ አደባባይ እስከ መገናኛ ባለው መንገድ ላይ ከመኪናዎች ጋራ እየተጋፉ ሲመላለሱ ቢታዩ አይደንቅምን? ይደንቃል;። ምክናያቱም ጥማድ በሬዎቹ እርሻው ቦታ ላይ መገኘት ስለነበረባቸው ነው። የእርሻ ሚኒስቴር ሠራተኞችም እንደዛው።፡
የመብራት ኃይል ሠራተኞች መስመሮችን እየተከታተሉ ካልሠሩ ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለው በወረቀት ላይ ብቻ ቢሠሩ እንዲት ነው የመብራት ችግር የሚቀረፈው? ታዲያ የተማረው ችግሮችን የሚያባብስ ከሆነ ካልተማረው በምን ይለያል? አንተ ይህንን ጽሑፍ የምታነብ ወገኔ በተመደብክበት ሙያ ለኅብረተቡ ምን ለውጥ አመጣህ? እኔም እንዳንተው የወር ደሞዜን ከመጠበቅ በስተቀር ምንም ለውጥ አላመጣሁም ነበር። ነገር ግን ከዚህ በኋላ አንድ ነገር ማድረግ እንችላለን። ልጆቻችንን ፣ የልጅ ልጆቻችንን ትምህርት ቤት ስንልክ ለምን እንደሚማሩ በሚገባ ብናስረዳቸው ችግሮችን የሚያጠፉበትን መንገድ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ልናዘጋጃቸው እንችላለን።

